24/08/2026
ግዙፉን ስታዲየም ወደ ቀደመ ግርማው!🏟️
የወልድያ ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየምን ከደረሰበት ጉዳት ጠግኖ ወደ አገልግሎት ለመመለስ የሚያስችል ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ስታዲየሙን ነጻ በማድረግ ጥገና እንዲደረግለት ለክልሉ መንግሥት ርክክብ ማድረጉን አሚኮ ከወራት በፊት መዘገቡ የሚታወስ ነው።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት ለስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል። በዚህም የስፖርት መሠረተ ልማቶች በተሻለ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሠራ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
በወልድያ ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
ለዚህም የክልሉ መንግሥት ቁርጠኝነቱን ወስዶ ለስታዲየሙ ጥገና የሚውል አስፈላጊውን በጀት መመደቡን አስታውቀዋል። ከቀጣይ መስከረም 2019 ዓ.ም ጀምሮ ጨረታ በማውጣት የጥገና ሥራው እንደሚጀመርም ገልጸዋል።
ከጥገና ሥራው ጎን ለጎን በከተማዋ ተጨዋቾችን እና የስፖርት ቤተሰቡን ማስተናገድ የሚችሉ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲሟሉ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የእንግዳ ማረፊያዎች እና ሌሎችም የአገልግሎት መስጫ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ከከተማ አሥተዳደሩ እና ከባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
ይህንን መሠረት አድርገው ወደ ሥራ የገቡ ባለሃብቶች መኖራቸውንም ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል። ሌሎች ባለሃብቶችም በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ እንዲያለሙ ጥሪ የማድረግ እና ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው የአሚኮ ዲጂታል
15/08/2026
የባህር ዳር ስታዲየም ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ጊዜያዊ ፈቃድ አገኘ
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቅርቡ በባህር ዳር ስታዲየም ላይ ያደረገውን ፍተሻ እና ግምገማ ተከተሎ ብሄራዊ ቡድናችን በመስከረም ወር 2019 በሜዳው ለሚያደርገው ጨዋታ የሚያገለግል ጊዜያዊ የካቴጎሪ 3 (CAT 3) ፈቃድ መስጠቱን ዛሬ ለኢ/እ/ፌ በላከው ደብዳቤ አስታውቋል። ይህ ጊዜያዊ ፈቃድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚጠብቀውን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሜዳው ጨዋታን በሀገሩ እንዲያደርግ ያስችለዋል።
ካፍ በስታዲየሙ የተመዘገቡ መሻሻሎችን በማድነቅ በላከው ደብዳቤ አሁንም ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጿል። የተቆጣጣሪ ቡድኑን ግኝቶችና የሚቀሩ የማስተካከያ እርምጃዎችን የያዘ ሙሉ ቴክኒካዊ ሪፖርት በቅርቡ ለፌዴሬሽኑ እንደሚላክ ገልፆ ጨዋታው በሚደረግበት ቀን የስታዲየሙን ዝግጁነት እና የደንቦች አተገባበር ለመከታተል የስታዲየም ተቆጣጣሪ ሊመድብ እንደሚችልም አስታውቋል።
ካፍ አያይዞም ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለስታዲየሙ አስተዳደር እና ለሚመለከታቸው አካላት በሂደቱ ላደረጉት ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።
03/08/2026
እየተተከሉ ያሉ ችግኞችን በዘላቂነት እንክብካቤ የሚያደርግ ባለቤት እየተፈጠረ መሆኑን መምሪያው አሳወቀ።
ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም (ወልድያ ኮሙኒኬሽን)
በወልድያ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ቃል ተጠናክሮ መቀጠሉን የወልድያ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ ደስታ ሞላ አስታውቀዋል።
በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በከተማ ውስጥ በቋሚ ፍራፍሬ ላይ ትኩረት ማድረጉን የገለፁት ወ/ሮ ደስታ የተተከሉ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ለታለመላቸው ዓላማ ደርሰው ጥቅም እንድሰጡ እንክብካቤ የሚያደርግ ባለቤት መፈጠሩን አስታውቀዋል።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ያስጀመሩት የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ዋና ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ከተማችንን አረንጓደ ከማልበስ ባሻገር አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ማተኮራችን ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል።
ከተተከሉ ችግኞች መካከል በ7 ወር ጊዜ ጥቅም የሚሰጥ የፓፓያ ዝርያ አንዱ መሆኑን ከመምሪያው
ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
29/07/2026
የክረምት ፉትሳል ውድድር በወልድያ ከተማ በይፋ ተጀመረ
ወልድያ፣ ሀምሌ 22/2018 ዓ.ም
በወልድያ ከተማ አስተዳደር እቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ 03 አድማስ ባሻገር ቀበሌ በየጁ ገነት ሜዳ፣ ስፖርት ለሰላም በሚል መሪ ሃሳብ እና የቀድሞውን የጉቤ ስፖርት ክለብ ተጫዋች ይመር ጌታቸውን ለማሰብና ለማክበር የተዘጋጀው የክረምት ፉትሳል ውድድር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
ውድድሩ ከሀምሌ 22 እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በተከታታይ የሚካሄድ ሲሆን፣ 5 የማስ ስፖርት ቡድኖችና 8 የኤ ቡድኖች በድምሩ 13 ቡድኖች በውድድሩ ይሳተፋሉ።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የወልድያ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሪት ነፃነት አንበሳው እና የ03 አድማስ ባሻገር ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አማረ በመገኘት ውድድሩን በይፋ አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅት ወ/ሪት ነፃነት አንበሳው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ውድድሩ የወጣቶችን የስፖርት ተሳትፎ ከማሳደግ ባሻገር የአንድነት፣ የሰላምና የወንድማማችነት እሴቶችን የሚያጎለብት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም የይመር ጌታቸውን መልካም ስምና ለስፖርቱ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ውድድሩ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።
በተመሳሳይ የ03 ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አማረ፣ ውድድሩ ወጣቶችን በስፖርት ዙሪያ በማሰባሰብ ከአሉታዊ ተግባራት እንዲርቁ፣ የመከባበርና የፍትሃዊ ውድድር ባህል እንዲያዳብሩ እንዲሁም ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች እንዲታወቁ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
የውድድሩ አዘጋጅ አቶ ዘመኑ አጋዤ በበኩላቸው፣ ይህ የመታሰቢያ ውድድር በድንገት ህይወቱ ላለፈው ይመር ጌታቸው ያለውን ክብርና ፍቅር ለመግለጽ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም የይመር ጌታቸው መልካም ባህሪ፣ ስፖርታዊ ሥነ-ምግባርና ትጋት ለወጣቱ ትውልድ አርአያ እንዲሆን ይህ ውድድር በየዓመቱ እንዲካሄድ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል። በተጨማሪም ተሳታፊ ቡድኖች በፍትሃዊ ውድድር፣ በመከባበርና በወንድማማችነት መንፈስ እንዲወዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ወ/ሪት ነፃነት አንበሳው፣ ይህ የፉትሳል ውድድር ወደ ሌሎች ክፍለ ከተሞችም እንዲስፋፋና ቀጣይነት እንዲኖረው መምሪያው የሚያስፈልገውን ሁሉንም ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም ውድድሩ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በፍጹም ሰላማዊና ስፖርታዊ የፉክክር መንፈስ እንዲካሄድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
19/07/2026
ከሁለት ሳምንት በላይ ሲካሄድ የቆየው የከተማ አስተዳደሩ የማስ ስፖርት ውድድር በዛሬው ዕለት ፍጻሜዉን አግኝቷል።
ሀምሌ 12/2018 ዓ.ም (ወልድያ ኮሚኒኬሽን)
ለተከታታይ ሁለት ሳምንት ሲካሄድ የቆየዉ የማስ ስፖርት ዉድድር በደማቅ ሁኔታ ዛሬ ፍጻሜዉን አግኝቷል።
በዉድድሩ 12ት ቡድኖች የተሳተፉበት ሲሆን ለፍጻሜዉ ጉቤ እና አልበንጀር የተገናኙ ሲሆን አልበንጀር ጉቤን 4ለ1 በሆነ ሰፊ ዉጤት በማሸነፍ የድሉ ባለቤት ሁኗል።
በዉድድሩ የመዝጊያ መርሃ ግብር የተገኙት የወልድያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የተከበሩ አቶ ዱባለ አብራሬ ስፖርት ለከተማ ገጽታ ግንባታ ሚናዉ ከፍተኛ ነዉ። ስለሆነም ከተማ አስተዳደራችን ለስፖርቱ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የመልካ ቆሌን የስፖርት ሜዳ አሁን ካለበት ወደ ተሻለ የስፖርት ማዘዉተሪያ ለማሳደግ አየሰራ እንደሆነ እና በቅርቡም ወደ ስራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከንቲባዉ አያይዘዉም የሼህ ሙሐመድ ሑሴን አሊ-አላሙዲን ስታዲየምም የክልሉ መንግስት ከፍተኛ በጀት ይዞለት በ2019 በጀት አመት የጥገናዉ ስራ እንደሚሰራ እና በቀጣይ ሀገራችን ለሚኖራት አህጉር አቀፍ ዉድድር ዝግጁ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ስለሆነም መሰል የማስ ስፖርት ዉድድሮችም ተጠናክረዉ መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሪት ነጻነት አንባሰዉ ውድድሩ የከተማችን የስፖርት ማህበረሰብ ከማነቃቃት ባለፈ፣ በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ፍቅርና ትስስር ይበልጥ ያጠናከረ እንደሆ ገልጸዋል ።
ኃላፊዋ አክለዉም በርካታ ቁጥር ያለው ደጋፊ ስታዲዬም ተገኝቶ የተመለከተው የውድድር መድረክ እንደነበር ገልጸዉ ለቀጣይ ከዚህ ላቀ ባለ መልኩ ለማዘጋጀት እና የተሳታፊዉንም ቁጥር ለመጨመር አቅደዉ እየሰሩ እንደሆነ አብራርተዋል ።
የከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ስንታየሁ ብርሃን እንዳሉት የስፖርት ዉድድሩ ጨዋነትን የተላበሰና በርካታ ተመልካችን ያስተናገደ እንደነበር ገልጸዋል።
ዉድድሩ መቀራረብን ቤተሰባዊነትን የፈጠረ ሲሆን ይሄም ዉድድር ተጀምሮ እንዲፈጸምም በርካታ አካላት የቡኩላቸዉን ኃላፊነት ተወጥተዋል ብለዋል።
የሐረር ቢራ አክሲዮን ማህበር ወልድያ ቅርንጫፍ በብዙ መልኩ ለስፖርት ዉድድሩ ድጋፍ እንዳደረገ የተቋሙ ተወካይ አቶ ምህረቱ የማታዉ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በስፖርት ዉድድሩ ለተሳተፉ አካላት ፣ ለተሳተፉ ክለቦች እና ግለሰቦች የእዉቅና ሰርቲፊኬት የገንዘብ እና የዋንጫ ሽልማት የተበረከተላቸዉ ሲሆን የዉድድሩ ሻምፒዮን የሆነዉን አልበንጀር የዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት የተበረከተለት ሲሆን ሽልማቱንም ከእለቱ የክብር እንግዳ ከተከበሩ አቶ ዱባለ አብራሬ እጅ ተረክቧል።
አቶ ንጉስ ዝናቡ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ፣ አቶ ዝናቡ ሰጠ የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ አስራት በሪሁን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊና አቶ አሰፋ መስፍን የከተማ አስተዳደሩ መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ በዕለቱ በእንግድነት ተጋበዘዉ ተገኝተዋል።
19/07/2026
የወልድያ ከተማ የማስ ስፖርት ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን ያገኛል! 12/11/2018
«የማስ ስፖርት የእግር ኳስ ውድድር» በ12 ቡድኖች በድምቀት ከተጀመረ ከ2 ሳምንት በላይ ያስቆጠረው ይህ ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን ያገኛል።
አልበጅር 🆚 ጉቤ
ውድድሩ የከተማችን ስፖርት ከማነቃቃት ባለፈ፣ በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ፍቅርና ትስስር ይበልጥ ያጠናከረ ነው። በርካታ ቁጥር ያለው ደጋፊ ስታዲዬም ተገኝቶ ለቀናት ጨዋታዎችን ታድሟል።
ለተከታታይ በድምቀት ሲካሄድ የሠነበተው ውድድር በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን ያገኛል አልበጅር 🆚 ጉቤ ቡድን 3:00 ሰዓት ለዋንጫ ፍልሚያ አገናኝቷል።
ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ 2:00 ሠዓት መቶ አምፖል 🆚 ህብር ለደረጃ የሚጫወቱ ይኾናል።
18/07/2026
የወልድያ ፖሊቴክኒክ ኮሌጁ 28ኛ ዙር ሰልጣኞችን አስመርቋል።
ሐምሌ 11/2018ዓ.ም
በዛሬው ዕለት የወልድያ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ከደረጃ 2 እስከ ደረጃ 5 በ8 በተለያዩ የሙያ መስከ ያሰለጠናቸውን 240 ሰልጣኞች አስመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የወልድያ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን የተከበሩ አቶ ሙሉጌታ ምስጋናው ሰልጣኞች በተመረቁበት የሙያ ዘርፍ የያዙትን እውቀትና ጉልብት ተግባር ላይ በማዋል የሀገራችንና የአካባቢያችንን ጸጋ በመጠቀም ለራስም ሆነ ለሀገርም ጠቃሚ እንዲሆኑ ለተመራቂዎች አሳስበዋል፡፡
በምርቃ መርሐ-ግብሩ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳ የወልድያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ዋና ከንቲባ እና የኮሌጁ የቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ዱባለ አብራሬ ተመራቂዎች የሥራ ፈጠራ ዕድል የክህሎት ባለቤት መሆን ማለት የአሰሪን ፊት መመልከት ብቻ ሳይሆን የራስን የሥራ ዕድል በመፍጠር ሌሎችን ለመቅጠር የምትችሉ ናችሁና እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ከተመራቂዎቹ መካከል በትምህርት ክፍሏም በአጠቃላይ የግቢ የትምህርት ክፍሎችም 3.92 በማምጣት ሁለት ዋንጫ፣ ሜዳልያ የወሰደችው ተማሪ እየሩስ ሲሳይ ዜና በውጤቱ መደሰቷን ገልጻለች፡፡
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ (ICT) ተመራቂዋ እየሩስ ለውጤቱ መላቅም የራሷ ጥራት፣ የቤተሰቦቿና የመምህራኖቿ ድጋፍ ምክንያት መሆኑን አስረድታለች፡፡
በምርቃ መርሐ-ግብሩ በበጀት ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም የተሻለ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሥራ ቡድኖች፣ የሥልጠና ክፍሎች እና ግለሰቦች እውቅና ተሰጥቷል፡፡
የወልድያና ሀራ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የጉባላፍቶ ወረዳ አስተዳደር የሥራ ክህሎት ሥልጠና ተቋማት ተወካዮች በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ሰልጣኞችን የሰነድና የአካል ርክክብ ሥነ-ስርዓት ፈጽመዋል።
አውቶሞቲቭ፣ ግብርና፣ ቴክስታይልና ጋርመንት፣ ሰርቪይንግና ድራፍቲንግ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ፣ኤሌክትሪክሲቲ ኤሌክትሮኒክስ፣ መንገድ ሰራ ፣ሕንጻ ምህንድስና ሰልጣኞች ከተመረቁባቸው የሙያ ዘርፍ ናቸው።
ምንጭ:- ወልድያ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ህዝብ ግንኙነት ነው
10/07/2026
የመልካቆሌ ስፖርታ ሜዳ የዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ፕሮጀክት ዲዛይን ለግምገማ ቀረበ።
ሐምሌ 3/2018 ዓ.ም (ወልዲያ ኮሙኒኬሽን)
በወልድያ ከተማ አስተዳደር በመልካቆሌ ስፖርት ሜዳ ሊገነባ የታቀደው ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ፕሮጀክት ዲዛይን ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ በዝርዝር ተገምግሟል።
ፕሮጀክቱ ለወጣቶች፣ ለህፃናት እና ለመላው የከተማዋ ነዋሪዎች ዘመናዊ የስፖርትና የመዝናኛ አገልግሎት በመስጠት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በጤናው ዘርፍ በርካታ ጥቅሞችን ለማስገኘት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የወልድያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ የተከበሩ አቶ ዱባለ አብራሬ በንግግራቸው፣ ፕሮጀክቱ በከተማዋ የስፖርት መሰረተ ልማትን ከማጠናከር ባሻገር ወጣቶችና ህፃናት ጊዜያቸውን በጠቃሚ ተግባራት እንዲያሳልፉ፣ ከአልባሌ ቦታዎችና ከአሉታዊ ተፅእኖዎች እንዲርቁ እንዲሁም በአእምሮና በስነ-ልቦና የበሰለ ትውልድ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ከንቲባው አክለውም ፕሮጀክቱ የከተማዋን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊና እድገት ለማፋጠን የሚያስችል ትልቅ የልማት ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሻራ ኢንቴሪየር ዲዛይን የቀረበው ይህ የፕሮጀክት ዲዛይን በውስጡ የእግር ኳስ ሜዳ፣ የወጣቶች ማገገሚያ፣ የቅርጫት ኳስ ፣ የመረብ ኳስ ሜዳዎች፣ የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎች እና ሌሎች የመዝናኛና የስፖርት አገልግሎት መስጫዎችን እንደሚያካትት ተጠቁሟል።
በግምገማው የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው፣ ከተማዋ ለረጅም ጊዜ ስትፈልገው የነበረ ፕሮጀክት ወደ ተግባር ሊሸጋገር መሆኑ አስደሳች መሆኑን ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ለከተማዋ እድገትና ለወጣቶች ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዲዛይኑ የበለጠ እንዲሟላ ሌሎች ደጋፊ መሠረተ ልማቶች እንዲካተቱ ምክረ ሀሳቦችን አቅርበዋል።
ከንቲባው በማጠቃለያ ንግግራቸው ለፕሮጀክቱ የቀረቡት ሁሉም አስተያየቶች ገንቢ መሆናቸውን በማንሳት ፕሮጀክቱ ያለንን የበጀት አቅም ባገናዘበ መልኩ በቅርቡ ወደስራ እንደሚገባና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደሚጀመሩ ጠቁመዋል።
03/07/2026
የወልድያ ከተማ ባህል ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ የ2018 ዓም የማስ ስፖርት ውድድር የመክፈቻ ፕሮግራም በደማቅ ሁኔታ ተጀመሯል።በወጣለቸው ፕሮግራም መሠረት የተካሄዱ ውድድሮች ውጤት
✍️መቶ አፖል ሰሜን ወሎ 5ለ1
✍️አልበንጀር አርበኞቹን 3ለ1
ከሰዓት በኋላ
✍️መድህን ሆስፒታል ማረሚያ ቤትን 4ለ0
በቀን 26/10/2018 የሚከናወን ጨዋታ
ኤሌክትሪክ 🆚 ንግድ ባንክ 10:00 ሰዓት ላይ በመልካቆሌ ሜዳ ይጫወታሉ
02/07/2026
መምሪያው በአብዛኛዎቹ የሥራ ዘርፎች ከዕቅዱ በላይ የሆነ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አስታወቀ።
ሰኔ 25/2018 ዓ.ም (ወልድያ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን)
የወልድያ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ በ2018 ዓ.ም ያከናወናቸውን የሥራ አፈጻጸሞች የሚያሳይ ዓመታዊ ሪፖርት ዛሬ ለአመራሮችና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት አቅርቦ፣ በአብዛኛዎቹ የሥራ ዘርፎች ከዕቅዱ በላይ የሆነ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አስታውቋል።
በሪፖርቱ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ዮናስ ቢምር ባቀረቡት ሪፖርት፣
በውስጥና በውጭ ኢንስፔክሽን ሥራዎች፣ በግንዛቤ ፈጠራ መርሃ ግብሮችና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
አያይዘውም ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ ክፍያ በጠየቁ አሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
በ2018 ዓ.ም 44 የትራፊክ አደጋዎች መከሰታቸውንና ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ማሳየቱን የቀረበው ሪፖርት ያመላክታል።
የታክሲ ስምሪትና የታሪፍ ቁጥጥርን ማጠናከር፣ ድንገተኛ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ፍተሻ ማካሄድ እንዲሁም የብዙኃን ትራንስፖርትን ማሳደግ የቀጣዩ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ሃላፊው በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው፣ ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ ክፍያ እንዳይፈጸም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እንዲጠናከሩ፣ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች የታሪፍ ቁጥጥር ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ እንዲሁም የሕግ ማስከበር ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።
የወንጀል መከላከል ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ሁነኛው ምህረቱ፣ በዓመቱ ውስጥ በሁሉም የሥራ ዘርፎች የተቀናጀ ሥራ መከናወኑ ገልፀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በተሻለ አፈጻጸም ቢከናወኑም፣ የትራፊክ አደጋዎች መጨመራቸው በሥራው ተጨባጭ ውጤት ላይ ተጨማሪ ግምገማ እና ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ ያመለክታል ነው ያሉት።
አክላውም በታሪፍ ጥሰት ላይ የሕግ ማስከበርን ማጠናከር፣ ድንገተኛ የተሽከርካሪዎች ፍተሻ ማካሄድ፣ የትራፊክ ደህንነት ምክር ቤት ማቋቋም እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን ከተጨባጭ ለውጥ ጋር ማስተሳሰር በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የወልድያ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ የተከበሩ አቶ ዱባለ አብራሬ በማጠቃለያ ንግግራቸው፣ መምሪያው በ2018 ዓ.ም ያስመዘገበውን አፈጻጸም በማድነቅ ለህብረተሰቡ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት እንዳስመዘገበ ገልጸዋል።
ከንቲባው በቀጣይ የዘርፉን አፈጻጸም ለማሻሻል ጠንካራ የቅንጅትና የትብብር ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን ማሻሻል፣ የህዝብ ትራንስፖርትን የበለጠ ተደራሽ ማድረግ፣ እንዲሁም የCCTV ካሜራ ቴክኖሎጂን በስፋት በመጠቀም ሕገ-ወጥ አሰራሮችን መከላከልና የህብረተሰብ ተሳትፎን በማጠናከር ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ማከናወን የቀጣይ ትኩረት ሊሆኑ የሚገቡ ቁልፍ አቅጣጫዎች መሆናቸውን አሳስበዋል።
በመጨረሻም በ2018 ዓ.ም በዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።