30/07/2026
> የፕሮጀክቱ መስራች❗
👇🏽
ለጎቲያ ካፕ ወደ ስዊዲን ከሄዱ የኢትዮጵያ ቡድኖች መካከል ደብል ፓስ የእግር ኳስ ፕሮጀክት አንዱ ነው፤ ከቀሩት ተጫዋቾች አብዛኞቹ ከዚህ ስብስብስ የተገኙ በመሆናቸው ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጠን የፕሮጀክቱ መስራች ታዲዮስ ተክሉ ጋር ደውለን ተከታዩን ቆይታ አድርገናል፥ እነሆ፦
🎤 ታዲዮስ ስለ ትብብርህ በቅድሚያ እናመሰግናለን፤ ስለራስህና ስለ ፕሮጀክታችሁ በማስተዋወቅ እንጀምር እስኪ?
"ጉዳዩን ለማጥራት ስለደወልክልኝ ታምሩ እኔም አመሰግናለሁ፤ ታዲዮስ ተክሉ እባለሁ፤ የቀድሞ ተጫዋች የአሁን አሰልጣኝ ነኝ፤ ከጫካ ሜዳ ፕሮጀክት ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡና፣ ንግድ ባንክና ኤሌክትሪክ ታዳጊ ቡድኖችን አሰልጥኛለሁ፤ የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኜም በሴካፋ ተሳትፌያለሁ፤ አሁን ደግሞ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሴቶች ቡድንን አሰለጥናለሁ፤ በተጨማሪ የደብል ፓስ ፕሮጀክት መስራችና ዋና አሰልጣኝ ነኝ፤ ይህ ፕሮጀክት ከተቋቋመ ዘጠኝ አመት ሆኖታል፤ በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር ተመዝግበን በከተማው ከ20 አመት በታች ውድድር ላይ እንሳተፋለን"
🎤 የስዊዲን ጎቲያ ካፕ እድልን እንዴት አገኛችሁ?
"በራሳችን ጥረት ተፃፅፈን ነው እድሉን ያገኘነው፤ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የተሳተፍነው፤ ከዚህ ቀደም ዴንማርክ ላይም ውድድር አድርገናል"
🎤 እስኪ ስለ ስዊዲን ጉዟችሁ አጫውተን
"18 ተጫዋቾችንና 4 የአሰልጣኝ አባላትን በጥቅሉ 22 ልዑካንን ይዘን ነው የሄድነው፤ በውድድሩም ጥሩ ተሳትፎ ነበረን"
🎤 22 ሆናችሁ ሄዳችሁ ስንት ሆናችሁ ተመለሳችሁ?
"1 ተጫዋችና 3 የአሰልጣኝ አባላት በአጠቃላይ 4 ሰዎች ብቻ ነው ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው፤ 18ቱ አልመጡም"
🎤 ይህ እንዴት ሊፈጠር ቻለ?
"የሁላችንም መመለሻ ቀን ውድድሩ ከተጠናቀቀ ከሁለት ቀን በኋላ ነበር፤ ሆኖም የአንዱ ታዳጊ ተጫዋች የቅርብ ቤተሰብ ሰርግ ሀምሌ 12 ስለነበር ወላጆቹ ቶሎ ቢመጣልን አሉን፤ በእድሜው ምክንያት ብቻውን መላክ ስለማንችል እኔና ሁለት የአሰልጣኝ አባላት እንዲሁም ተጫዋቹን ጨምሮ አራት ሆነን ትኬታችንን አስተካክለን በፍፃሜው ቀን ቅዳሜ ሀምሌ 11/2018(ጁላይ 18/2026) ወደ አዲስ አበባ ተመለስን፤ ቀሪዎቹ 18ቱ ሰኞ ሀምሌ 13 ነበር የመመለሻ ቀናቸው፤ እኛ አዲስ አበባ ሳንደርስ ለትራንዚት በቆየንበት ኳታር ሆነን ግን ተጫዋቾቹ ቡድናችን ካረፈበት ትምህርት ቤት ሳያሳውቁ እንደወጡ ተነገረን"
🎤 ከዛ ምን አደረጋችሁ?
"ወዲያው ለአዘጋጆቹ አሳወቅናቸው፤ እነሱም ለመረጃው አመስግነውን ለሚመለከተው የፀጥታ አካል እንሳውቃለን አሉን፤ አዲስ አበባ ከደረስን በኋላ ድጋሚ አንዷ የቡድን መሪ ጋር ስደውል እንደማይመለሱ፥ ተጫዋቾቹንም ስዊዲን የሚኖሩ ቤተሰብና ዘመዶቻቸው እንደወሰዷቸው ነገረችን፤ ኢትዮጵያ ያሉ ወላጆችንም ጠየቅን፤ ልጆቹ ያሉበትን ቦታ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም፤ ይህንንም ለአዘጋጆቹ በድጋሚ አሳውቀናል፤ ከ10 ቀን በኋላ ዜናውን አወጡት"
🎤 ይህ እንዳይከሰት ቅድሚያ ዝግጅት አላደረጋችሁም?
"በደንብ አድርገናል፤ ውል አዘጋጅተን የሁሉንም ተጫዋቾች ወላጆች አስፈርመናል፤ ስዊዲን ከደረስን በኋላም የሁሉም ተጫዋቾች ፓስፖርት እኔ ጋር ነበር፤ ሆኖም እኔ ቀድሜ መመለስ ስለነበረብኝ ፓስፖርቱን ለቡድን መሪ ሰጠሁ፤ ተያይዘው ቀሩ፤ ውስጥ ውስጡን በደንብ ተዘጋጅተውበት ነበር"
🎤 ለመሆኑ ወጪያችሁን የሸፈነው ማነው?
"የተጫዋቾቹን የጉዞ ወጪ የቻሉት ወላጆቻቸው ናቸው"
🎤 ምን ያህል ከፈሉ?
" ለስልጠና፣ ለጉዞና ለተለያዩ አቅርቦቶች እያንዳንዳቸው 300ሺህ ብር ከፍለዋል፤ የተሻለ አቅም ያላቸው ደግሞ 400ሺህ ብር ከፍለው አግዘውናል"
🎤 ለምን 400ሺህ ብር?
"የመክፈል አቅም የሌላቸውን ሶስት ያህል ተጫዋቾችን ይዘን ሄደናል፤ የእነሱን ወጪ ደግሞ እኛና አቅም ያላቸው ወላጆች ሸፍነናል፤ ወላጆቹ ከ300ሺህ ብር በተጨማሪ 100ሺህ ብር እየጨመሩ 400ሺህ ብር እየከፈሉ አቅም የሌላቸው ተጫዋቾች እንዲሄዱ አግዘውናል"
🎤 ከተጫዋቾች በተጨማሪ ወላጆችስ ሄደዋል?
"አዎ ሁለት ተጫዋቾች ከእናቶቻቸው ጋር አብረው ወደ ስዊዲን ሄደዋል"
🎤 እና ተመለሱ?
"ሁለቱም ተጫዋቾችም ሆኑ እናቶቻቸው አልተመለሱም"
🎤 ተጓዥ ተጫዋቾች ከእግርኳስ ጋር ያላቸው ግንኙነትና ችሎታ ደካማ የሆኑ፥ የባለሀብትና የባለስልጣን ልጆች ናቸው ይባላል እውነት ነው?
"ፕሮጀክታችን በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንና በፊፋ ኮኔክት የተመዘገበ ነው፤ ሆኖም እድሜያቸው ከ16 አመት በታች ስለሆኑ ችሎታ ላይ ብቻ የተመሰረተ ምልመላ አናደርግም፤ ይህን መሰል አለም አቀፍ ውድድር ላይ ስንሳተፍ ደግሞ ቪዛ ለማግኘት አንዱ መስፈርት የወላጆቹ ኢኮኖሚያዊ አቅም ይታያል፤ ስለዚህ የባለሀብትም የባለስልጣንም ልጆች ይኖሩናል፤ ከቀሩት ውስጥ ግን የባለስልጣን ልጅ የለም"
🎤 የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተጫዋቾቹ መጥፋት አዝኛለሁ ሆኖም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባላት አይደሉም ብሎ መግለጫ አውጥቷል፤ ምን ትላለህ?
"እንዳልኩህ በራሳችን ጥረት ነው ተሳትፎውን ያገኘነው፤ ከብሄራዊ ቡድን ጋርም አይገናኝም፤ በተፈጠረው ነገር ዋነኛ ተጎጂዎችም እኛ ነን፤ ስማችን ላይ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፤ በጣም አዝነናል"
🎤 በድጋሚ ለትብብርህ ላመስግንህና የመጨረሻ ጥያቄ ላንሳ፥ የቡድኑ ፎቶ ላይ አንድ ህፃን ልጅ ይታያል፤ ተጫዋች ነው?
"ኸረ አይደለም፤ የእኔ ልጅ ነው፤ ገና ስድስት አመቱ ነው፤ አብረን ሄደን አብረን ተመልሰናል"
★ ማስታወሻ፦ ከደብል ፓስ ፕሮጀክት በተጨማሪ በአሰልጣኝ እድሉ ደረጄ የሚመራው ኢዲዋይ እና ዳን አቢሲኒያ የተባሉ ቡድኖች በስዊዲን ጎቲያ ካፕ ተሳትፈዋል፤ እነሱም ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀን ምላሻቸውን እየጠበቅን ነው
(ታምሩ ዓለሙ)
29/07/2026
⭕️ሽመልስ በቀለ እና ሀዋሳ ከተማ በይፋ ተለያዩ
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ከታዩ ድንቅ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆን የቻለው ሽመልስ በቀለ ከሀዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን ከተገኘ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ደግሞ በግብፅ ሊግ ላሉ በርካታ ክለቦች በመጫወት አስደናቂ አመታትን ማሳለፍ ችሏል።
ከሁለት አመት በፊት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለመቻል እና እንዲሁም ደግሞ ለአሳደገው ክለብ ሀዋሳ ከተማ የሁለት አመት ኮንትራትን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በመፈረም በይፋ መቀላቀል የቻለ ቢሆንም በክለቡ በተፈጠሩ ያለ መግባባት የተነሳ ከሳምንታት በፊት ያስገባው የመልቀቂያ ደብዳቤ ተቀባይነት በማግኘቱ ከክለቡ ጋር የአንድ አመት ውል እየቀረው መለያየቱን ሀገሬ ቴሌቪዥን ከክለቡ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
29/07/2026
⭕️20 ኢትዮጵያውያን ተጨዋችች ስዊድን ላይ መጥፋታቸውን የስዊድን ፖሊስ አስታወቀ!
👇🏽
በስዊድን ጎተንበርግ በተካሄደው ዓመታዊ የጎቲያ ካፕ የእግር ኳስ ውድድር ላይ ከተሳተፉ በኋላ ከኢትዮጵያ የመጡ 20 ተጨዋችች እና የቡድን አባላት መጥፋቸዉን የ ስዊድን ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው። እንደ ፖሊስ ገለጻ፣ የጠፉት ተጫዋቾቹ ከ14 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ያላቸው መሆኑን ገልፆ ወደ ኢትዮጵያ አለመመለሳቸዉ የተረጋገጠ ሲሆን ፍለጋዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይሆናል ተብሏል።
በተለይም የጠፉት የቡድኑ ተጨዋችች ከ18 አመት በታች ከመሆኑ ጋር ተደምሮ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይስ ሌላ የሚለዉ ሂደቶች በማጣራት ላይ መሆኑን ፖሊስ ተናግረዋል።
27/07/2026
⭕️የሊጉ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፈረመ
ከሀድያ ዞን ሾኔ ከተማ የተገኘው እና በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በግሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተሳካ ጊዜ ያሳለፈው ናትናኤል ዳንኤል ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፈርሟል።
የ2017 የውድድር ዘመን አጋማሽ በከፍተኛ ሊጉ ቤንች ማጂ ቡና ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የተቀላቀለው እና በውድድር ዘመኑ ከፋሲል ከነማው አጥቂ ታምራት እያሱ ጋር በእኩል 15 ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ነበር ያጠናቀቀው።
ፈረሰኞቹ ከአጥቂው በተጨማሪ የብሩክ ታረቀኝ እና ፀጋ ከድርን ውል ለተጨማሪ አመት አራዝሟል።
27/07/2026
⭕️መቐለ 70 እንደርታ በፊፋ ታገደ
በ2017 የውድድር ዘመን መቐለ 70 እንደርታን ከተቀላቀሉ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች መካከል ካሜሮናዊው አጥቂ ማንይክሬ ዳንጉሞ አንዱ ነው።
የሳይፕረሱን ክለብ የንካሚ ኤኬን ለቆ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሞዓም አናብስቱን የተቀላቀለው ይህ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በክለቡ ቆይታ ማድረግ የቻለ ሲሆን ብዙም አመርቂ ጊዜን በክለቡ ማሳለፍ ባይችልም ክለቡ ያልከፈለኝ ደመወዝ አለ ብሎ ለፊፋ በማመልከቱ ክለቡ ለተጫዋቾቹ እስከሚከፈል ድረስ መታገዱን አገሬ ስፖርት ያገኘዉ መረጃ ይጠቁማል።
በያዝነው አመት መቐለ 70 እንደርታ ከፕሪምየር ሊጉ መውረዱም ይታወሳል።
27/07/2026
⭕️የጦና ንቦቹ ሀይጃክ ወይስ ...
ወላይታ ድቻ ከደቂቃዎች በፊት ሴኔጋላዊውን የመሀል ተከላካይ አዳማ ዋድን ለማስፈረም መስማማቱን ጠቁሟል።
194 ሴ.ሚ የሚርዝመው ተከላካዩ ባለፉት ሁለት አመታት ላይ የሴኔጋሉን ኃያል ክለብ ጃራፍን በአምበልነት ቡድኑን መርቷል።
በ2024/25ም ቡድኑ የሴኔጋል ሊግ ሻምፒዮን ሲሆን የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ነበር። ሻምፒዮን ለመሆን ያስቻለውንም ወሳኝ ግብ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ አስቆጥሯል።
በተጨማሪም የ2024 የሴኔጋል የቻን ቡድን ዝግጅት ላይ አምበል ጭምር የነበረ ቢሆንም በዋናው ውድድር ላይ አብሮ አልተጓዘም።
ይህ ተጫዋች ታድያ በዓመቱ መጨረሻ ከጃራፍ ጋር ከተለያየ በኋላ ያሙሶክሩ የተሰኘ ክለብን ለመቀላቀል መስማማቱን የሀገሬው ሚዲያዎች ዘግበው ነበር።
Transfer Market ላይም ጭምር ከ26 ቀናት በፊት ጀምሮ የያሙሶክሩ ተጫዋች መሆኑን ይገልጻል።
አዳማ ዋድ ከአስር ቀናት በፊትም ክለቡ ያማሶክሩ የፈረንሳዩን ኦሊምፒክ ማርሴይን አቢጃን ላይ በገጠመበት የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል።
በተጨማሪም ወላይታ ድቻ ሱሌማን ሀሚድን እና የኪዳኔ አሰፋን ውል በሁለት ዓመታት ለማራዘም መስማማቱን ይፋ አድርጓል።
Mitiku
24/07/2026
⭕️የዋልያዎቹ አምበል በሰፈር ውድድር ዳኛ ደበደበ!
: የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) አምበል ጋቶች ፓኖም፣ በክረምት የሰፈር ውድድር ላይ ከጨዋታ ዳኛ ጋር በገባው አለመግባባት ዳኛውን መደብደቡ በማህበራዊ ሚዲያ እና በእግር ኳሱ ቤተሰብ ዘንድ ትልቅ ቁጣ እና ውዝግብ አስነስቷል።
እንደ መረጃዎች ገለጻ፣ ተጫዋቹ በክረምቱ እረፍት ወቅት በተዘጋጀ የሰፈር ውድድር ላይ ተሳትፎ እያደረገ በነበረበት ወቅት፣ በመሀል ዳኛው ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ቀይ ካር ተሰጥቶታል። በዚህ ሁኔታ የተበሳጨው ጋቶች ወደ ዳኛው በማቅናት አካላዊ ጥቃት አድርሷል። ተጫዋቹ ድርጊት ሲፈፅም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት ተሰራጭቷል።
ድርጊቱም በስፍራው የነበሩ ተመልካቾችን እና የስፖርት አፍቃሪዎችን በእጅጉ ያስገረመና ያሳዘነ ሆኗል። የጋቶች ፓኖም ድርጊት ይፋ ከሆነ በኋላ በርካታ ደጋፊዎች፣ ስፖርት ጋዜጠኞች እና የእግር ኳስ ተንታኞች ተጫዋቹን አጥብቀው እየኮነኑት ይገኛሉ።
ጋቶች የሀገርን ትልቅ የብሔራዊ ቡድን አምበልነት በጥቁር እና ቢጫ ማሊያ የሚመራ፣ ለታዳጊዎች እና ለወጣት ተጫዋቾች መልካም አርኣያ (Role Model) መሆን የሚገባው አንጋፋ ተጫዋች ሆኖ ሳለ፣ በሰፈር ጨዋታ ላይ እንዲህ አይነት የስነ-ምግባር ጉድለት ማሳየቱ ጨርሶ የሚጠበቅ አይደለም ሲሉ ተችተውታል።
በፕሮፌሽናል ደረጃ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የተጫወተ ልምድ ያለው ተጫዋች፣ የስፖርታዊ ጨዋነት ህግጋትን ማክበር ሲገባው በቁጣ ተሸንፎ ዳኛ ላይ እጅ
ለማንሳት መሞከሩ የሙያው ስነ-ምግባር አበክሮ ያፈነገጠ መሆኑን የብዙዎች አስተያየት ያመለክታል።
23/07/2026
⭕️የኖርዊች ሲቲ ክለብ ተጫዋች አሊ አህመድ ከሸገር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ጋር አብሮ እንደሚሰራና ለክለቡ አለም አቀፍ እገዛ እንደሚያደረግ ገለፀ!
ትውልደ ኢትዮዽያዊው አሊ አህመድ በቀጣይ የሸገር ከተማ እግር ኳስ ክለብ አለማቀፋዊ ጉዞውን እውን ለማድርግ የራሱን ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጿል።
ምስረታውን ካደረግ አጭር ጊዜን ያስቆጠረው የሸገር ከተማ እግር ኳስ ክለብ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም፣ ክለቡን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ፣በውጪው አለም የጨዋታ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር እና ዘመናዊ የክለብ አደረጃጀት ተሞክሮን ለመውሰድ የራሱን ድርሻ እንደሚወጣም ይጠበቃል።
የካናዳ ብሔራዊ ቡድን አባልና እና የኖርዊች ሲቲ ክለብ ተጫዋች አሊ አህመድ በዛሬው ዕለት የከተማው ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ሀላፊነቱን ወስዷል።
አሊ የሸገር ከተማ ምልክት ያለበት የክብር ሽልማት የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ አዱኛ በተገኙበት የተበረከተለት ሲሆን፣ ይህም ለከተማዋ እግር ኳስ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው እና የሸገር ከተማን እግር ኳስ ክለብ ዓለም አቀፋዊ ጉዞ እና የክለቡን የረጅም ጊዜ እቅድ እውን እንደሚያደርግ ተገልጿል።
23/07/2026
⭕️የ2019 የኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቼ ይጀመራል?
የኢትዬጵያ ብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ጨዋታዎች እና የአዲሱ ዓመት የኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግ
ጠቅላላ ጉባኤው አዲስ ቀን አግኝቷል
ክለቦች በይፋ መስኮቱ ከመከፈቱ አስቀድሞ በተጨዋቾች የዝውውር ስራ ተጠምደው በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት አወዳዳሪው አካል የአዲሱ ዓመት ሻምፒዮና የሚጀመርበትን ግዜ ይፋ ለማድረግ መቃረቡን በተለይ ለወርልድ ለስፓርት የደረሰው መረጃ አመላክቷል።
ከወዲሁ እየወጡ ያሉት መረጃዎች የ2019 የኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግ መስከረም ወር ይጀመራል በማለት ቢጠቁሙም አወዳዳሪው አካል ግን ሊጉ የሚጀመርበትን ቀርጥ ያለው ቀን በቀጣይ ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግ አረጋግጠናል።
ፕሪምየር ሊጉ በዝናብ መፈተኑ እና ክለቦች ለኢንተርናሽናል ዉድድር በቂ የመመዝገቢያ ግዜ እንዲያገኙ በተጨማሪ በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ጨምሮ በርካታ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ስለሚጠብቀው ሊጉን በግዜ መጀመር እንደሚገባ ወርልድ ያነጋገረቻቸው የክለብ አመራሮች ጠቁመዋል።
የኢትዬጵያ ብሄራዊ ቡድን በመስከረም ወር ብቻ ከሱዳንና ከሴኔጋል ጋር የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ስለሚያደርግ ፕሪምየር ሊጉ በመስከረም የመጀመሩን ነገር ሲበዛ አጠራጣሪ ያደርገዋል።
ዋሊያዎቹ እስከ መጋቢት የአፍሪካ ዋንጫ ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ ስለሚያደርጉ ፕሪምየር ሊጉ ይሄንን ታሳቢ ያደረገ መርሃ ግብር ያስፈልገዋል።
በሌላ በኩል የፊታችን እሁድ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጠቅላላ ጉባኤ ለቀጣይ ሳምንት ቀን ተይዞለታል።
ወርልድ እንዳረጋገጠችው ትላልቅ ውሳኔዎች የሚጠበቁበት ጠቅላላ ጉባኤ የዛሬ ሳምንት ሃምሌ 23/2018 ይካሄዳል።ለክለቦችም ደብዳቤ ደርሷቸዋል።
@ወርልድ ስፖርት
22/07/2026
➖️"በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው የሚጫወቱበትን አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል:"- ትውልደ ኢትዮጵያዊው አሊ አሕመድ
👇
የኢትዮጲያ እግርኳስ ፌደሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች አሊ አህመድ ጋር ውይይት አካሂደዋል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዲያስፖራ ተጨዋቾችን የመቀላቀል ሂደትን ወደ ሀገራችን ለማምጣት ከመንግስት ጋር ንግግር እንደተጀመረ የገለፁ ሲሆን አሊ አህመድ በዚህ ረገድ ለሌሎች ትውልደ ኢትዮጲያዊያን ተጨዋቾች ላይ ተነሳሽነት መፍጠር እንዲችል ጥሪ አቅርበውለታል።
አሊ በበኩሉ ከሱ ውጪ ብዙ ቁጥር ያላቸው ትውልደ ኢትዮጲያዊያን እንዳሉ ገልፆ ዲያስፖራ ተጨዋቾች ወደ ሀገራቸው መጥተው የሚጫወቱበትን አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ሀገሬ ስፓርት ዘግቧል