12/08/2026
ሮናልዶ ለሜሲ የላከው መፅናኛ!❤
በእግር ኳስ ዓለም ለዓመታት የዘለቀውና የታሪክ ትልቁ ተቀናቃኝነት፣ በሀዘን እና በሰብአዊነት ፊት ቦታውን ለፍቅርና ለክብር ለቋል።
ሊዮኔል ሜሲ የአባቱን የጆርጌ ሜሲ ህልፈት ተከትሎ በኢንስታግራም ገፁ ባሰፈረው ልብ የሚነካ የስንብት ደብዳቤ ብዙዎች አፅናንተውታል። ይህንን የሜሲን የሀዘን እሳት ያየው የቅርብ ተቀናቃኙ ክርስቲያኖ ሮናልዶ—አባትን ማጣት ምን ያህል ከባድና ጥልቅ ቁስል እንደሆነ በራሱ ህይወት ያውቀዋልና ባለበት ቦታ ሆኖ ለሜዳ ላይ ተቀናቃኙ የማፅናኛ መልእክቱን አስፍሯል።
ሮናልዶ በሜሲ የስንብት ደብዳቤ ስር ባሰፈረው መልእክት፡ "በዚህ ከባድ ወቅት ላንተና ለቤተሰቦችህ ታላቅ እቅፍ ይድረሳችሁ፣ ሌኦ። በርታ!" ብሎታል።
ይህ መልእክት የመጣው ሮናልዶ ከባለቤቱ ጆርጂና ሮድሪጌዝ ጋር ህጋዊ ጋብቻውን አፅድቆ በደስታ ላይ በነበረበት ቅጽበት ቢሆንም፣ የሰው ልጅ ሀዘን ከማንኛውም ደስታና እግር ኳሳዊ ተፎካካሪነት በላይ መሆኑን አሳይቷል።
የሜዳ ላይ ፍልሚያና የዋንጫ ሽሚያ ሲያበቃ፣ ሁለቱ የእግር ኳስ ኮከቦች በመከራ ቀን አብሮ የመቆምን ታላቅነት ዳግም አስመስክረዋል። በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት ውብ አጋጣሚዎች አንዱ የሆነው ይህ የሮናልዶ መልእክት፣ ከፉክክር ይልቅ ሰብአዊነትና መከባበር ሁልጊዜም እንደሚያሸንፍ ህያው ማረጋገጫ ነው።❤🥹👏
10/08/2026
🚖❤️ ብራዚላዊው የመሀል ሜዳ ሞተር ብሩኖ ጊማራኤስ በሰውነቱ ላይ የተቀረፀውና ጀርባው ላይ ያረፈውን 39 ቁጥር ማለያ ለአዲሱ ክለቡ አርሰናል ከፈረመ በኋላ ሲናገር "ታክሲዋ ለቤተሰቤ ሁሉንም ነገር ሰጥታናለች፤ መኖሪያ ቤታችንን፣ የእለት ምግባችንን፣ አልባሳታችንን... ሁሉንም ነገር ያገኘነው በዚያች ታክሲ ነው!"
አባቱ በብራዚል ጎዳናዎች ላይ ለ20 ዓመታት ያህል የታክሲ አሽከርካሪ ሆነው ሲሰሩ፣ የቤተሰቡን ህይወት ያቀኑት 39 ቁጥር ታክሲያቸውን እየነዱ ነበር። ብሩኖም የአባቱን የዓመታት ድካም፣ መስዋዕትነት እና ለቤተሰቡ የሰጠውን ፍቅር ለመዘከር በሄደበት ሁሉ ይህንን ቁጥር በክብር ይዞት ይዞራል!
አሁን ደግሞ ይህንን የአባቱን መታሰቢያ የሆነውን የክብር ቁጥር በመድፈኞቹ ቤት ኢሚሬትስ ማግኘቱን ገልጾ፣ በደስታና በኩራት ስሜቱን አጋርቷል። የአባት ፍቅርና መስዋዕትነት ውጤት... ቁጥር 39! 🔴⚪️✨
10/08/2026
የእግር ኳስ ንጉሡ “ወርቃማ እግሮች”!
እኤአ በ1981 በታዋቂዋ ፎቶግራፈር አኒ ላይቦቪዝ ካሜራ የተቀናጨበችው ይህች የማትረሳ ምስል፣ የዓለምን የእግር ኳስ ንጉሥ የፔሌን እግሮች ፍፁም ተፈጥሯዊና ጥበብ በተሞላበት መንገድ ታሳያለች።
የእግሮቹ በጭቃ መሸፈን፣ የቆዳው መሸብሸብና የለፋበት ምልክት ሁሉ—ሕይወቱን ሙሉ ኳስን ከእግሩ ሥር ሳያርቅ ያሳለፈውን ድንቅ ሰው ሙሉ የሕይወት ጉዞና ታሪክ በዝምታ ይተርካሉ።
በወቅቱ ፔሌ ለፎቶግራፈሯ አኒ ሲናገር፤ በልጅነቱ የእግር ኳስ ጫማ ጨርሶ እንደልነበረውና ለብዙ ዓመታት በባዶ እግሩ ይጫወት እንደነበር አውግቷታል። በመሆኑም አዳዲስ የስፖንሰር ጫማዎችን አድርጎ ከመቆም ይልቅ፣ ጫማዎቹን አውልቆ እውነተኛ ማንነቱንና መነሻውን በሚገልፀው ባዶ እግሩ ፎቶውን ለመነሳት መረጠ። እነሆ… ፔሌን የዓለም እግር ኳስ "ንጉሥ" ያደረጉት ጥንካሬና ታሪክ ያረፈባቸው እግሮች እነዚህ ነበሩ! 👑❤️
09/08/2026
የሴዑሉ ድራማና አስደናቂው ፍልሚያ!
: በስፖርቱ ዓለም አንዳንድ ድሎች በሰከንዶች ልዩነት ይመዘገባሉ፤ ሌሎች ደግሞ የመላው ዓለምን ትኩረት የሚስቡ ድራማዎችን ጥለው ያልፋሉ። እኤአ በ1992 በደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል የተካሄደው የዓለም ወጣቶች (ከ-20 ዓመት በታች) አትሌቲክስ ቻምፒዮና ግን ሁለቱንም አስተናግዷል። የዓለም ወጣት ከዋክብት በየሁለት ዓመቱ ሲፋለሙ ያ የሴኡል ስታዲየም ትዝታ ሁልጊዜም በአትሌቲክስ አፍቃሪዎች ልብ ውስጥ ይታደሳል።
በዚያ ታሪካዊ ምሽት በ10ሺ ሜትር ማራኪ ፍልሚያ አብዛኛውን 25 ዙር በሙሉ ጉልበትና ፍጥነት ሲመራ የቆየው ብርቱው ኬንያዊ ጆሴፍ ማቹካ ነበረ። ከስተጀርባው እግር በእግር እየተከተለ፣ የታክቲክ ድሩን በጥንቃቄ ሲሸምን የቆየው ደግሞ ገና በዓለም መድረክ ስሙ ያልገነነው የ19 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ወጣት—ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር።
የውድድሩ ማጠቃለያ ሲቃረብ የሴኡል ስታዲየም በጩኸትና በጭብጨባ ተናጋ። በመጨረሻዎቹ 50 ሜትሮች ላይ ኃይሌ ባልተጠበቀ መብረቃዊ ፍጥነት ማቹካን ቀድሞት መፈተለክ ጀመረ። የያዘውን አንደኝነትና የወርቅ ሜዳሊያ በድንገት የተቀማው ማቹካ፣ በድካምና በቁጣ እራሱን መቆጣጠር አቃተው። ኃይሌ የድሉን መስመር ለመርገጥ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩት፣ ማቹካ ከኋላው በኃይል ጀርባውን በቦክስ ነረተው!
ይህ አጋጣሚ በወቅቱ ትልቅ መነጋገሪያ ሆነ። ኃይሌ በ28:03.99 በመግባት የወርቅ ሜዳሊያውን ሲያጠልቅ፣ ማቹካ ግን ባሳየው ያልተገባ ስፖርታዊ ባህሪ ምክንያት ወዲያውኑ ከውድድሩ ተሰረዘ፤ የብር ሜዳሊያውንም ተቀማ። ኃይሌ በዚሁ ውድድር በ5ሺ ሜትርም ኢስማኤል ኪሩይንና ሂቻም ኤልግሩዥን የመሳሰሉ የዓለም ታላላቅ አትሌቶችን አስከትሎ በመግባት ድርብ ወርቅ በማሳካት የዓለምን ትኩረት በሙሉ ወደ እራሱ ሳበ። ይህ ኩነት የበርካታ ኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት እንዲሆንና የረጅም ርቀት ሩጫ ንጉሥ እንዲባል ያደረገው ወርቃማ ታሪኩ መነሻ ሆነ።
የዚህ አጋጣሚ እውነተኛ ውበት ግን በውድድሩ ማጠናቀቂያ ላይ አላበቃም። የሁለቱ አትሌቶች ከውድድር በኋላ የነበራቸው ምላሽና የበሰለ አመለካከት የስፖርቱን ትክክለኛ መንፈስ ያሳየ ነበር። ኃይሌ ድርጊቱን ሁልጊዜም በፈገግታ እያስታወሰ "ምቱ ይበልጥ ገፍትሮኝ መስመሩን በፍጥነት እንድሻገር አድርጎኛል" በማለት በወቅታዊ ስሜት የመጣ እንጂ በክፋት እንዳልሆነ ይገልጻል።
ከአትሌቲክስ ህይወቱ በኋላ በንግድና በእርሻ ስራ የተሰማራው ማቹካ፣ በወቅቱ ያሳየው ስሜታዊነት የስፖርት ስነ-ልቦናና የታክቲክ ስልጠና ማነስ ያስከተለው ስህተት እንደነበር አምኗል። ሁለቱ አትሌቶች ከዓመታት በኋላ ይቅርታ በመጠያየቅ ጥብቅ ወዳጅነት መሥረተዋል፤ ያንን የሴኡል ድራማዊ ምሽትም በጋራ እየሳቁ የሚያስታውሱት ትዝታ አድርገውታል።
በዚያች የሴኡል ምሽት ኃይሌ ጀርባ ላይ ያረፈው "ቦክስ" ቂም ያዘለ ትዝታ ሆኖ አልቀረም፤ ይልቁንም የስፖርቱን ትልቅነት፣ የይቅርታን ግርማ እና የአንድን ታሪካዊ አትሌት ወርቃማ ዘመን ያበሰረ ድቅድቅ ትዝታ ሆኖ በታሪክ መዝገብ ላይ ተቀርጿል።
09/08/2026
✨በኦሪገን የደመቁት የነገ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ተስፋዎች!
🏃 🇪🇹 : በአሜሪካዋ ኦሪገን ግዛት፣ ዩጂን ከተማ ላለፉት ቀናት የዓለምን ትኩረት ስቦ የሰነበተው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዛሬ ሌሊት ፍፃሜውን ያገኛል። ከ147 ሀገራት የተውጣጡ ብርቱ አትሌቶች በተሳተፉበት በዚህ ታላቅ መድረክ፣ የኢትዮጵያ ወጣት አትሌቶች ሀገራቸውን በታላቅ ኩራት በማስጠራት ድንቅ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
አርብ ሌሊት በተካሄደው የሴቶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ወጣቶች በወርቅና ብር ሜዳሊያዎች መድረኩን አድምቀውታል። በውድድሩ የመጨረሻዎቹ አስደናቂ ሰከንዶች በተደረገው ብርቱ ፉክክር፣ አትሌት አልማዝ ዮሐንስ በበሰለ የታክቲክ አሯሯጥና በሚያስገርም ፍጥነት ርቀቱን በ9:15.81 በመጨረስ የወርቅ ሜዳሊያው ባለቤት መሆኗ ይታወቃል። ሌላኛዋ ተስፈኛ አትሌት ወሰኔ አሰፋ በበኩሏ አስደናቂ ብቃቷን በማሳየት በ9:30.50 ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያውን ስታጠልቅ፣ የኬንያዋ አትሌት አናታሻ ቼፕቶ በ9:37.18 ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያ ወስዳለች።
በተመሳሳይ ዛሬ ማለዳ በተካሄደው የሴቶች 3ሺህ ሜትር (ቀጥታ) የፍፃሜ ውድድር ላይም የኢትዮጵያውያኑ ተስፈኛ ኮከቦች የበላይነት ቀጥሏል። አትሌት ዮርዳኖስ ፅጋብ በድንቅ የአጨራረስ ብቃት 8:43.65 የሆነ አዲስ የግል ምርጥ ሰዓቷን በማስመዝገብ ለሀገሯ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አበርክታለች። በቻምፒዮናው የመጀመሪያ ቀን በ5ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው ሌላኛዋ ተስፈኛ ኮከብ አትሌት ሽቶ ጉሚ፣ የ3ሺህ ሜትሩን ፉክክር በ8:45.06 ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያ አሳክታለች። በዚህ ውድድር ዩጋንዳዊቷ አትሌት ቻሪቲ ቼሮፕ በ8:45.59 የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።
በሌሎች ርቀቶችም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል። በሴቶች 800 ሜትር የፍፃሜ ውድድር አትሌት ሀብታም ገበየሁ በ2:03.99 አራተኛ ደረጃን፣ አትሌት ደራርቱ ሽብሩ በ2:04.81 ሰባተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በወንዶች 5ሺ ሜትር የርምጃ ውድድር አትሌት ነገሮ አዱኛ 20:22.82 የሆነ የግል ምርጥ ሰዓቱን በማስመዝገብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።
ቻምፒዮናው ዛሬ ሌሊት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በ1500 ሜትር ፍፃሜ በሁለቱም ፆታዎች ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን ትጠበቃለች። በሴቶች 1500 ሜትር (ምሽት 5:52 ሰዓት) ሐረገወይን ካላዩ እና ኤልሳቤት አማረ ለሜዳሊያ ይጠበቃሉ። በማጣሪያው በምድብ ሁለት የተወዳደረችው ሐረገወይን ካላዩ 4፡12.54 ሁለተኛ ሆና ወደ ፍፃሜው ስታልፍ፣ በምድብ ሶስት ማጣሪያዋን ያደረገችው ኤልሳቤት አማረ በበኩሏ 4፡18.24 በሆነ ሰዓት ከምድቧ 1ኛ ቀዳሚ በመሆን ፍፃሜውን መቀላቀሏ ይታወቃል።
በወንዶች 1500 ሜትር (ምሽት 6:25 ሰዓት) አትሌት ደስታው ታዴ በብቸኝነት ኢትዮጵያን ይወክላል። አትሌት ደስታው በማጣሪያው በ3:34:03 4ኛ በማጠናቀቅ ለፍፃሜው ፍልሚያ የበቃ ጠንካራ ተፎካካሪ ነው። እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች ከ147 ተሳታፊ ሀገራት 35ቱ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል። አሜሪካ 8 ወርቅ፣ 6 ብር እና 4 ነሐስ (በድምሩ 18 ሜዳሊያዎች) መሪነቱን ስትይዝ፣ ጣሊያን 3 ወርቅ እና 2 ነሐስ (በድምሩ 5 ሜዳሊያዎች) ትከተላለች። ኢትዮጵያ በ2 ወርቅ፣ 3 ብር እና 1 ነሐስ (በድምሩ 6 ሜዳሊያዎች) ሦስተኛ ላይ ተቀምጣለች።🇪🇹✨
08/08/2026
"አልማዝን አይቼ ...አልማዝን ባያት..!"
🇪🇹🏃በዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር፣ የኢትዮጵያ የነገ ተስፋዎች ፍፁም የበላይነታቸውን አሳይተዋል። ተፎካካሪዎቿን በሩቅ ጥላ በ9:15.81 ሰዓት ውድድሩን በድል ያጠናቀቀችው አትሌት አልማዝ ዮሐንስ የወርቅ ሜዳሊያውን ስታጠልቅ፣ ሌላኛዋ አትሌታችን የብር ሜዳሊያውን በማስገኘት የድሉን ማዕረግ አደመቁት።
ይህች አዲሷ አልማዝ ዮሐንስ የሩጫውን መድረክ ስትቆጣጠር፣ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ድሏ ብቻ አልነበረም፤ የያዘችው ስምና ያሳየችው ድንቅ ብቃት ሌላኛዋን ታሪካዊ አትሌት አልማዝ አያናን አስታውሳናለች!
የዓለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮኗ አልማዝ አያና ወደ 5ሺ እና 10ሺ ሜትር በመሸጋገር የዓለም አትሌቲክስን ከመቆጣጠሯ በፊት፣ መነሻዋ ይኸው የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር ነበር። በሪዮ ኦሊምፒክ ለሁለት አሥርታት ያህል ሳይደፈር የቆየውን የ10 ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ ሰባብራ አዲስ ታሪክ ስትፅፍ፣ በተለየ አሯሯጧና በተፎካካሪዎቿ ላይ በምታሳየው ፍፁም የበላይነት መሳ አልነበራትም።
አሁን ደግሞ በወጣቶች ቻምፒዮና አዲሷ ኮከብ አልማዝ ዮሐንስ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ያሳየችው አስደናቂ ብቃትና በራስ መተማመን፣ ከቀድሞዋ አልማዝ ጋር በስም ብቻ ሳይሆን በግብርም ተስፋ የሚጣልባት ኮከብ መሆኗን ያሳየ ነው። ይኸው ድል አልማዝ ዮሐንስ የዛሬ የወርቅ ባለቤት ብቻ ሳትሆን፣ የቀጣዩ የኢትዮጵያ የረጅም ርቀት ንግሥትና የታላቋ አልማዝ አያና ትክክለኛ ተተኪ መሆኗን ለዓለም ፍንጭ የሰጠችበት ሆኗል!🇪🇹💪
08/08/2026
ዓለም እንዲህ ናት! አንዱ በደስታ፣ ሌላው በመሪር ሀዘን!
💔 የዓለምን የእግር ኳስ መድረክ ላለፉት ሁለት አሥርታት በጋራ ሲነግሱበትና በድንቅ ፉክክራቸው ሲያደምቁት የኖሩት ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ዛሬ ፍፁም ባልተጠበቀና ተቃራኒ በሆነ የስሜት ማዕበል ውስጥ ይገኛሉ። ህይወት በአንድ ገጽ ላይ ተስፋና ደስታን፣ በሌላው ገጽ ደግሞ መሪር ሀዘንን አስፍራ ተከሰተች።
በአንድ በኩል፣ የሊዮኔል ሜሲ ቤተሰብ በከባድ ሀዘን ተውጧል። የዓለም ኮከቡ አባትና የቅርብ አማካሪ ሆርሄ ሜሲ በ68 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሆርሄ ሜሲ ለሊዮኔል ወላጅ አባት ብቻ አልነበሩም፤ በልጅነቱ ያጋጠመውን የዕድገት ሆርሞን እክል ተቋቁሞ ወደ ባርሴሎና እንዲያቀና መንገድ የከፈቱ፣ በየእግር ኳስ ዘመኑ ሁሉ በወኪልነትና በአማካሪነት ከአጠገቡ ያልተለዩ የህልሙ ዋና ሞተር ነበሩ። ያንን ታላቅ ኮከብ ለዓለም ያበረከቱት ጠንካራ አባት ማለፍ ለሜሲ እጅግ የከበደና ልብ የሚሰብር ነው።💔
በሌላኛው የዓለም ጥግ ደግሞ፣ የሮናልዶ መንደር በደስታ ደምቃለች። ክርስቲያኖ ሮናልዶ በተቃራኒው በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት በትውልድ ሀገሩ ማዴራ ደሴት ለማከናወን የመጨረሻ ዝግጅቱን ጨርሶ በደስታ ማዕበል ውስጥ ይገኛል።
ላፉት ዓመታት በሜዳ ላይ ድንቅ ውድድር ሲያሳዩን የኖሩት ሁለቱ ታሪካዊ ኮከቦች፣ ዛሬ ደግሞ የህይወትን ሁለት ተቃራኒ ገፆች በአንድ ቀን እያስተናገዱ ነው። አንዱ በትውልድ ደሴቱ ላይ የፍቅርና የደስታን አክሊል ሲደፋ፣ ሌላኛው ደግሞ የህልሙ መሰረት የሆኑትን አባቱን አጥቶ በሀዘን ይቆዝማል። ዓለም እንዲህ ናት፤ በአንድ ጀምበር ለአንዱ ፈገግታን፣ ለሌላው ደግሞ ዕንባን ታድላለች!!
08/08/2026
⚡️⚽️💔 እግር ኳስ የብዙ ሚሊዮኖች ህይወት፣ ስሜትና ደስታ ነው። አንዳንዴ ግን ይህ ውብ ስፖርት በሰከንዶች ቅፅበት ለማመን ወደሚከብድ አሰቃቂ ትራጄዲ ሲቀየር ማየት ልብን ይሰብራል።
📍 የዛሬ 28 ዓመት ገደማ በ1998 ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው በኮንጎ የተከሰተው አጋጣሚ በስፖርቱ ታሪክ ውስጥ አሁንም ድረስ የሚያከራክር አሰቃቂ ክስተት ነው። ሁለት የኮንጎ ቡድኖች በጋለ ስሜት እየተጫወቱ በነበረበት ወቅት የወረደው አስፈሪ መብረቅ "ቤና ትሻዲ" የተባለውን ቡድን 11 ተጫዋቾች በቅፅበት ገድሎ ሜዳው ላይ ዘረራቸው።
የተጋጣሚውና የእንግዳው ቡድን ባሳንጋ አባላት ሙሉ በሙሉ ምንም ሳይሆኑ ከሜዳ መውጣታቸው አደጋውን ከአስማትና ጥንቁልና ጋር የሚያያይዙ መላምቶችን ፈጠረ። የሟቾቹ ክለብ ተጫዋቾች ያደረጉት ጫማ (ታኬታ) ብረት ያለው በመሆኑ መብረቁን ስቦት ሊሆን ይችላል ቢባልም፣ እስከዛሬ ግልጽ መደምደሚያ ሳይሰጠው ቀርቷል።
📍ተመሳሳይ አሳዛኝ አደጋ ሰሞኑን በደቡባዊ ታይላንድ፣ የሱንጋይ ጎሎክ ከተማ ሳንቲፋፕ ስታዲየም ተደግሟል። በጎሎክ ኤፍ ኤ ካፕ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ወቅት በጣለው ከባድ ዝናብ መብረቅ ወርዶ 13 ተጫዋቾች መሬት ላይ ተዘረሩ። 12ቱ ላይ ከባድ ጉዳት ሲደርስ፣ ከጥቂት ቀናት በፊት አዲስ ውል ተፈራርሞ የተስፋ ብርሃኑ እየፈካ የነበረው የ24 ዓመቱ አጥቂ ሰፍዋን አዋኤ ህይወቱ አልፏል።💔
እነዚህ አሳዛኝ አደጋዎች በከባድ አየር ንብረት ወቅት ጨዋታዎችን ማስቀጠል ስላለው አደጋ እና የተጫዋቾችን ደህንነት ማስጠበቅ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ለዓለም ስፖርት ትልቅ የማቂያወጫ ደወል ሆነዋል!
08/08/2026
🇪🇹🇪🇹እንኳን ደስ አለን‼️
🏃በዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የነገ ተስፈኛ ኮከቦች የዓለምን ትኩረት ስበዋል። በውድድሩ መጨረሻ ላይ በታየው ብርቱ ፉክክር አትሌት አልማዝ ዮሐንስ በድንቅ ፍጥነትና ብቃት ርቀቱን በ9:15.81 በመጨረስ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።
በተመሳሳይ አስደናቂ ብቃት ያሳየችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ወሳኔ አሰፋ ደግሞ በ9:30.50 ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳሊያውን ተጎናፅፋለች። የኬንያዋ አትሌት አናታሻ ቼፕቶ በ9:37.18 ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።🇪🇹🇪🇹
06/08/2026
ፓትሪክ ቪዬራ🗣 :-
"ሞሪንሆ ለሪያል ማድሪድ ትክክለኛው ሰው ሊሆን ይችላል? አዎ! ምክንያቱም እሱ የኮከብ ተጫዋቾችን አዕምሮ እንዴት ማሸነፍ እና ማስተዳደር እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል። እኔና ሞሪንሆ ሁልጊዜ አንስማማም ነበር፤ ነገር ግን ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ትክክለኛነቱን ተረዳሁ። ምክንያቱም እሱ እኔ ልሰማ የማልፈልገውን ነገር ግን ልሰማው የሚገባኝን መራር እውነት ፊት ለፊት ይነግረኝ ነበር።
ነገሩ እንዲህ ነው…
ማርች 2009 ላይ የማንቸስተር ዩናይትድ እና የኢንተር ሚላን ጨዋታ ነበረ። እኔ ገና ከጉዳት እየተመለስኩ ነበር፤ ሞሪንሆ ወደ እኔ መጥቶ፦ ‘ለዚህ ጨዋታ በቋሚ ተሰላፊነት እፈልግሃለሁ፤ 60 ደቂቃ ትጫወታለች’ አለኝ። ጨዋታው ተጀመረ። ገና በ4ኛው ደቂቃ ኔማንያ ቪዲች እኔን አልፎ በቴስታ ግብ አስቆጠረብን። እረፍት ሰዐት ላይ ስሜን የተቀያሪ ተጫዋቾች ሰሌዳ ተሠለከትኩ፣ እኔ ወጥቼ ሱሊ ሙንታሪ ገባ።
በነገታው በጣም ተናድጄ ወደ ሞሪኒሆ ቢሮው አመራሁ። ‘60 ደቂቃ ትጫወታለህ ያልከውን ቃል አላከበርክም!’ ብዬ ጠየቅኩት። እሱ ግን በተረረጋ መንፈስ አየኝና፦ ‘ጥሩ አልተጫወትክም። እኔ ደግሞ ለቡድኑ የሚበጀውን ውሳኔ መወሰን አለብኝ’ አለኝ።ዛሬ እኔ ራሴ አሰልጣኝ ሆኜ ሳስበው… ሞሪንሆ ያኔ መቶ በመቶ ትክክል ነበር!"